Jonah 4

ዮናስ እግዚአብሔር ምሕረት በማድረጉ ተቈጣ

1ዮናስ ግን ፈጽሞ አልተደሰተም፤ ስለዚህም ተቈጣ። 2ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁትስ ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመኰብለል የተነሣሁትም ለዚሁ ነበር፤ አንተ ቸርና ርኅሩኅ፤ ምሕረትህ የበዛ ከቍጣ የራቅህ አምላክ፣ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደ ሆንህ ዐውቃለሁ። 3አሁንም እግዚአብሔር ሆይ፤ ነፍሴን ውሰድ፤ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና።”

4 እግዚአብሔር ግን፣ “በውኑ ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው።

5ዮናስም ከከተማዪቱ ወጥቶ በስተ ምሥራቅ በአንድ ስፍራ ተቀመጠ። በዚያም ለራሱ ዳስ ሠራ፤ በከተማዪቱም የሚሆነውን ለማየት ከዳሱ ጥላ ሥር ተቀመጠ። 6እግዚአብሔር አምላክም የቅል ተክል አብቅሎ፣ የዮናስ ራስ ጥላ እንዲያገኝና ሙቀትም እንዳያስጨንቀው ከበላዩ እንዲያድግ አደረገ፣ ዮናስም ስለ ቅሉ እጅግ ደስ አለው። 7ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን በማለዳ እግዚአብሔር ትል አመጣ፤ ትሉም ቅሉን በላ፤ ቅሉም ደረቀ። 8ፀሓይ ስትወጣ፣ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ፤ ፀሓዩም የዮናስን ራስ አቃጠለ፤ እርሱም ተዝለፈለፈ፤ መሞትም ፈልጎ፣ “ከመኖር መሞት ይሻለኛል” አለ።

9እግዚአብሔር ግን ዮናስን፣ “በውኑ ስለ ቅሉ ልትቈጣ ይገባሃልን?” አለው።

እርሱም፣ “በርግጥ እስከ ሞት ልቈጣ ይገባኛል” አለ።

10 እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለው፤ “አንተ እንዲበቅል ወይም እንዲያድግ ላልደከምህበት ለዚህ ቅል እጅግ ዐዝነሃል፤ በአንድ ሌሊት በቀለ፤ በአንድ ሌሊትም ደረቀ። 11ታዲያ፣ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሶች ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?”

Copyright information for AmhNASV